የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፌዴሬሽን ም/ቤትና የክልል ም/ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክ በመቐለ፤

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴሬሽን ም/ቤትና የክልል ም/ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክ ከየካቲት 24 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በመቐለ ከተማ ተካሄዷል። በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት አስተባባሪነት የተሰናዳው ይህ የውይይት መድረክ ዋና አላማው በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር ነው። ለ14ኛ ጊዜ እንደ ተካሄደ የተነገረለት የአሁኑ መድረክ በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩሯል። ሁለቱ በምሁራን የቀረቡ የመወያያ ፅሁፎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ የፌዴራል የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ስርዓትና ተቋማዊ አደረጃጀት በወጣ ረቂቅ አዋጅና ዘንድሮ በተከበረው የ13ኛውን የኢትዮዽያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የእቅድ አፈጻጸምና የ14ኛው በዓል መነሻ እቅድ ላይ ውይይቱን አካሄዷል።

በመጀመሪያው ውሎው “አክራሪ ጎሰኝነት በኢትዮዽያ” እና  “የኢትዮዽያ ፌዴራል ስርዓት መነሻ እሳቤውና የዜግነት መብት” የሚሉ ፅሁፎች በዘርፉ ምሁራን ቀርበዋል። “አክራሪ ጎሰኝነት በኢትዮዽያ” በዶ/ር ዮናስ አዳዬ የተሰናዳ ነው ።ዶ/ር ዮናስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደሕንነት ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ የአክራሪነት ወይም የፅንፈኝነት መነሻው ከሌሎች ወደ ኋላ ቀርቻለሁ ፤ክብሬን አጥቻለሁ፤ ፍትሕ አልተከበረልኝም፣ መኖሬ ተረስቷል ከሚል እሳቤ እንደሚመነጭ ይናገራሉ። መገለጫውም በንፁሃን ዜጎች ላይ ስጋት፣ ፍርሃትና ጥርጣሬን መፍጠር ነው ይላሉ።

አክራሪ ጎሰኝነት አለም አቀፍ ይዘት እንዳለው የተናገሩት ዶ/ር ዮናስ በአንዱ አገር የተፈጠረው ችግር ለጉረቤትና አልፎ በርቀት ላሉ አገሮች ጭምር ህመም ስለሆነ ጉዳቱ ድንበር ተሻጋሪ እንደሆነ ይናገራሉ።

በአሁኑ ጊዜ የጎሳ ማንነት ከአገራዊ ማንነት እየጎላ በመምጣቱ ለጎሳ አክራሪዎች የተመቸ መደላድል እየፈጠረላቸው እንደሆነ ጠቁመው የጦር መሳሪያ በሕገ ወጥ መንገድ በገፍ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ደግሞ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

መፍትሔውም ይላሉ ዶ/ር ዮናስ የተማረ ማህበረሰብ መፍጠር፣ ማንነትን ያልዘነጋ አገራዊ አንድነትን ማጠናከር የሚችል ስርዓት መዘርጋት፣ ከጉረቤት አገሮች ጋር ያለን ግንኙነት ማጠናከርና ተቋማዊ ማድረግ፣ የሰላምን ባህል ማዳበር፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ የግጭቶች መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን አስቀድሞ ማምከን፣ የፌዴራልና የክልሎችን መዋቅር እንደገና መፈተሽና ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

ሌላኛው“ የኢትዮዽያ ፌዴራል ስርዓት መነሻ እሳቤውና የዜግነት መብት” በሚል ርዕስ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር አሰፋ ፍስሀ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ተቋም ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው።

እንደ ዶ/ር አሰፋ ገለፃ የአገራችን የፌዴራል ስርዓት ዋና መነሻው አሃዳዊ ስርዓቱ ባስከተለው የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና በማንነት መገለል ምክንያት ሕዝቦች ራሳቸውን የማስተዳደር፣ በሀገራቸው ጉዳይ የመሳተፍና የመወሰን ስልጣን ይኑረን፣ ማንነታችንና ቋንቋችን ይከበር በማለታቸው እንደሆነ ጠቁመው እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ብዙ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ከተካሄዱ በኋላ ሕገመንግሥቱ መፅደቁን አስታውሰዋል።

አክለውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “የዜግነት ፖለቲካ ብቻ” አስተሳሰብ ከአሁን በፊት ተገቢ ትኩረት ያላገኘና ክልሎችም በራስ ማስተዳደር ስም የዜጎች መብት አደጋ ውስጥ በማስገባታቸው፣ ክልሉም፣ መሬቱም በክልሉ የሚገኙ ተቋሞችም የዚያ ብሔር የሞኖፖል ንብረት አድርገው በማሰባቸው ምክንያት የመጣ እንደሆነ ገልጸው፣ መቀንቀኑ በጎ ነገር ቢሆንም “የዜግነት ፖለቲካ ብቻ” ብሎ ማሰብ ግን የወቅቱን አለም አቀፍና አገራዊ ሁኔታ በአግባቡ ያለመገንዘብ ችግር እንደሆነ አስገንዝበዋል።

እንደ ዶክተሩ አገላለፅ የዜግነት ፖለቲካ ብቻ የሚለው ርዕዮት የተለያዩ ትናንሽ ማንነቶች በትልቁ ብሔር እየተዋጡ ይሄዳሉ ከሚል ግምት የሚነሳና የዜጎች መብትና እኩልነት ከተከበረ የቡድን መብት አያስፈልግም የሚል ነው ካሉ በኋላ ይህ አስተሳሰብ አንዳንዴ የፌዴራል ስርዓት የሚቀበል ቢሆንም ሕዝቦች ራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ግን የማይፈቅድ እንደሆነ ተናግረዋል።

አያይዘውም የዚህ አስተሳሰብ ዋና ዓላማ ከብዙ ማንነቶች አንድ ማንነት መፍጠር የሚያስብና ለከፋፍለህ ግዛ እንዲመች አንዱን ብሔር በተለያዩ ክልሎች መከፋፈል ላይ ያተኮረ፣ በአጠቃላይ “ኢትዮዽያና ዜግነት ይቅደም፣ የብሔር ማንነት ይውደም!” የሚል ዕሳቤ የተሸከመ እንደሆነ ገልጸው፣ ሆኖም የብሔር መብቶችን በመደፍጠጥ የዜግነት ፖለቲካ ብቻ ለመጫን መሞከር አደጋው የከፋነው ብለዋል።

እንደ ጽሑፍ አቅራቢው አገላለጽ በአገራችን የፌዴራል ስርዓት ስራ ላይ መዋል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው በተለይ አንጻራዊ ሰላም፣ ተከታታይ የኢኮኖሚ፣ የመሠረተ ልማትና ማህበራዊ ዕድገት፣ የሕዝቦች የራስን በራስ የማስተዳደርና በሀገራቸው ጉዳይ የመሳተፍና የመወሰን መብት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

በማጠቃላያቸውም ምንም እንኳ የፌዴራል ስርዓቱ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችም ስኬቶች ማስመዝገብ ቢቻልም በየደረጃው ያሉ ተቋማት ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች አግባብነት ያለው መልስ መስጠት አለመቻል በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች እየተወሳሰቡ ወደ ግጭት እንዲገባ ምክንያት እንደሆኑ ሳይጠቁሙ አላለፉም።

በምክረ ሀሳባቸውም በየጊዜው ሪፎርም ማካሄድ፣ መሻሻል የሚገባቸውን ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና አሰራሮችን መፈተሽ፣ ተቋሞች ከድርጅት ተጽዕኖ ነፃ ማድረግ፣ በፌዴራልና በክልሎች ለሚደረጉ የልማት ስራዎች ክልሎችና ማህበረሰብን ማወያየት፣ ማሳተፍና ባለቤት ማድረግ፣ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች ማሳተፍ፣ በክልሎች የመወሰን ስልጣን ጣልቃ አለመግባት፣ ማንነቶችን የማይደፈጥጥ ኢትዮዽያዊነትን ማጎልበት፣ ክልሎች የዜጎችን መብት ያለመሸራረፍ ማክበር ግዴታቸው መሆኑን ማስተማርና ማስፈፀም እንደሚገባ ገልፀዋል።

ውይይቱን የመሩት የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምም መድረኩን ለተሳታፊዎች ክፍት ባደረጉት መሰረት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው በምሁራኑ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ከዚያም የተከበሩ አፈጉባኤ የብሄር ፖለቲካ አላማው የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብት ማስጠበቅ ነው፤ በዚህ ሂደት ግን የሌሎችን መብት ማክበር ይገባል። በተለይም አገራዊ ስሜትና ማንነት ሚዛን ጠብቀው መጓዝ ካልቻሉ አክራሪነት ይመጣል፤ አክራሪነት ወይም ፅንፈኝነት ደግሞ የጠባብነት ባህርይ ያለው በመሆኑ ወደ ጎጥ ከዚያም አልፎ ወደ ዝምድና ስለሚሄድ ማቋረጫ የለውም ብለዋል።

አያይዘውም አክራሪነትና ትምክህተኝነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን ጠቁመው የትምክህት ኃይል ግን ሁሉንም ጨፍልቆ የራሱ ያደርገዋል፤ የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰብ ራሳቸውን እንጂ ብሄር አይወክሉም በማለት ተናግረዋል።

እኔ አውቅልሀለሁ የሚል አመለካከት አደጋ አለው ያሉት የተከበሩ ወ/ሮ ኬሪያ ብሔርን ማነሳሳት ቀላል ነው፤ የትምሕርት ዝግጅትም አያስፈልግም፤ ሆኖም የብሄርና የዜግነት አክራሪነት ሁሉቱም አጥፊ ናቸው። በተለይም ራሱን በራሱ ማስተዳደር የለመደ ሕዝብ ወደ ዜግነት መቀየር አደጋ አለው ብለዋል።

በመጨረሻም የተከበሩ አፈጉባኤዋ የችግሩ መፍትሔ ከልዩነት ይልቅ አንድ በሚያደርጉ ላይ መስራት፣ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት፣ የአገርን ታሪክ የጋራ አድርጎ መቀበል፣ የባህልና የሃይማኖት ተቋማት በሰላም እሴቶች ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ በትብብር መስራት፣ የግጭት ምንጭ፣ መገለጫና ተዋንያን የሆኑትን በመለየት ችግሩን መፍታት ይገባል በማለት ተናግረዋል።