የጋራ ገቢዎች ከፋፈያ ቀመር ክለሳ ሥራ በመካሄድ ላይ ይገኛል፤

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሥራ ላይ ያለውን የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር የመከለስ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ እንደሚታወቀው ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(7) መሠረት የፌዴራል መንግሥቱ ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማ ከማከፋፈል በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥቱና የክልሎች የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎችም  በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን ቀመር የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ቀመር ላለፉት 16 ዓመታት ሲያገለግል የቆየ ሲሆን፣ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር መሻሻል ያለበት መሆኑን ምክር ቤቱ አምኖ የክለሳ ሥራው እንዲካሄድ መስከረም ላይ ባካሄደው ጉባኤው ወስኗል፡፡ 

በዚህም መሠረት፣ ቀመሩን በአዲስ መልክ የማዘጋጀት ሥራው የተጀመረ ሲሆን፣ ነባሩን ቀመር የመገምገምና አጠቃላይ የቀመር ዝግጅቱ ሥራ የሚመራበት የጥናት ፕሮፖዛል የማዘጋጀት ሥራም መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዝግጅቱ ሂደት የፌዴራል መንግሥቱንና የክልሎችን ሃሳብና አስተያየት ለማሰባሰብ የሚያስችል ምክክርም እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ፣ እስካሁን ድረስ የድሬዳዋ አስተዳደርን ጨምሮ የጥናት ቡድኑ ከትግራይ፣ ከሶማሌ፣ ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ከአፋር፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከሐረሪ ክልሎች የበላይ አመራሮች እና የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ውይይት በማካሄድ ጠቃሚ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ችሏል፡፡ በቀጣይም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች እንዲሁም ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ጋር ተመሳሳይ ሥራዎች ይከናወናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡