ግጭቶችን አስቀድሞ የመከላከልና ከተከሰቱም ለመፍታት

አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ስርዓቶች ከነበረችበት የግጭትና ብጥብጥ ታሪክ በመውጣት በፌዴራል ስርዓቱ አገግማ ዜጎቿ ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የሰላም አየር መተንፈስ ጀምረዋል፡፡ እርስ በእርስ በጥርጣሬ ከመተያየት ወጥተውም በልዩነት ውስጥ አንድ የጋራ አገር ለመገንባት ቃል ኪዳን ተግባብተው ወደ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ አቅንተዋል። ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን በተለያዩ አከባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡

የተጀመረዉን እድገትና ለዉጥ ለማስቀጠል፣ የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥና ግጭቶች አላስፈለጊ ጉዳት ሳያደርሱ አስቀድሞ መከላከል ይቻል ዘንድ ብሔራዊ የግጭት መከላከልና አፈታት ስትራቴጂ አዘጋጅቶ በሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት አማካይነት ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ካለችበት ሁኔታ አንጻር ቅድሚያ የሚሰጠዉ ትኩረት ነዉ፡፡ ግጭት ለመቀስቀስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በብቃት መመከት የሚቻለው ደግሞ መንስኤውን በትክክል መገንዘብ ሲቻል ነው፡፡ መንስኤውን በትክክል የለየ መፍትሄ ምን ጊዜም ቢሆን ግቡን ሳይመታ መቅረቱ የማይቀር ነው፡፡ ግጭቶች መልካቸውን እየቀየሩ ከመፈንዳታቸው በፊት ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ፣ ሁለንተናዊና ስትራቴጂያዊ የሆነ የግጭት መከላከልና አፈታት ስርዓት መዘርጋት ግጭቶቹን በፍጥነት ለመፍታት ከማገዙም በላይ ዳግመኛ እንዳይከሰቱና አስቀድሞ ለመከላከል ያግዛል፡፡

በዚህ ረገድ  የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተጣለበት ሕገ-መንግስታዊ ኃላፊነት በመነሳት ከዚህ ቀደም የተዘጋጀውን የግጭት ጥንቅር ካርታ ሰነድ ጥንካሬዎችንና ድክመቶችን በመፈተሸ የግጭት ተለዋዋጭ ባህሪንና አሁን አገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ስትራቴጂውን በመቅረፅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያላቸውን የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላትን በአዲስ መልክ እንደገና በማደራጀትና አገር አቀፍ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት በስትራቴጂው አስፈላጊነት ላይ በቂ ግንዛቤ በመፍጠር ሁሉንም አካላት ያሳተፈ የአብይ ኮሚቴ፣ የስራ አስፈፃሚና የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ያጠናቀቀ ሲሆን እስከአሁን ድረስ ከዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች መረጃዎችን የማሰባሰብ ስራ እየሰራን ሲሆን በቀጣይ መረጃዎችን የመተንተን፣ የግጭት ጥንቅር ካርታ የመስራት እንዲሁም ስትራቴጂውን የማዘጋጀትና ስትራቴጂውን የሚፈጽሙ አካላት ተለይተው ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች ተሰርተው ወደ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡