የኢፌዲሪ የመንግስታት ግንኙነት የፖሊሲ ማዕቀፍ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከቀድሞ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ከአሁኑ የሰላም ሚኒስቴር እንዲሁም የመንግስታት ግንኙነት ስርዓቱን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ካላቸው የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከሰራቸዉ አንኳር አገራዊ ስራዎች መካከል አንዱ የኢፌዲሪ የመንግስታት ግንኙነቶች የፖሊሲ ማዕቀፍ ነው፡፡

የመንግስታት ግንኙነት በፌዴራል ስርዓት ዉስጥ ብዙ ካልተዘመረላቸዉ የፌዴራል ስርዓት መገለጫ ባህሪያቶች ዉስጥ አንዱ ሲሆን የፌዴራልና የክልል መንግስታት በጋራ ወይም በጣምራ በተሰጣቸዉ ስልጣንና በሚያገናኟቸዉ ጉዳዮች ላይ የሚመሰርቱት መደበኛና መደበኛ ያልሆነ የግንኙነት ስርዓት ነዉ፡፡ ይህንን ግንኙነት በተመለከተ አንዳንድ የፌዴራል አገሮች ከመጀመሪያዉ ጀምሮ በሕገ-መንግስታቸዉ በግልጽ በመደንገግ እንዲሰራበት ያደርጋሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በሂደት በመደበኛ ሕግ በማስደገፍ ወደ መደበኛ የግንኙነት ማዕቀፍ እንዲሸጋገር ያደርጋሉ፤ ሌሎች ደግሞ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም የጋራ ፕሮግራሞችንና እቅዶችን በመንደፍ ቀላል በሆነ መንገድ ግንኙነቱ ወደ መደበኛ ስርዓት እያደገ እንዲሄድ ያደርጋሉ፡፡

ሀገራችን ያልተማከለ ፌዴራላዊ ስርዓተ-መንግስትን መከተል ከጀመረች ሁለት አስርተ ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ በእነዚህ ዓመታት የመንግስታት ግንኙነት የፌዴራል ስርዓታችን መገለጫ ባህሪይ በመሆን በስፋት ሲሰራበት ቆይቷል፤ በዚህም በርካታ የማይናቁ ዉጤቶችን አስመዝግበናል፡፡ ሆኖም የእስካሁኑ ልምዳችን በአንድ በኩል ግንኙነቶቹ በሁሉም ደረጃዎች የተሟላ ግልፅነት ያልተፈጠረበት መሆኑ፣ ሁሉን አቀፍ የግንኙነት ስርዓት አለመዘርጋቱ፣ በጋራ ሃላፊነት አለመመራቱ፣ የአሰራርና አደረጃጀት ዉስንነት የነበረዉ መሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ የግንኙነት ስርዓቱን የበለጠ ማጠናከር አስፈላጊ የሚያደርጉ አጀንዳዎች እየበዙ መምጣታቸዉ ያለፉት ዓመታት ልምዶቻችን አሳይተውናል፡፡

የመንግስት ስልጣን በየደረጃዉ ለሚገኙ የመንግስት እርከናት ተከፋፍሎ የተሰጠ ቢሆንም የሁሉም መንግስት ተልዕኮ አንድ ነዉ፤ እርሱም አስተማማኝ ዴሞክራሲ፣ ዘላቂ ሰላም፣ ፈጣን ልማትና ተከታታይነት ያለዉ ማህበራዊና ኢኮኖሚ እድገትን ማረጋገጥ ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ እዉን የሚሆነዉ በአንድ ወገን በሚደረግ ጥረት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም መንግስታት አብሮነትና ትብብር የሚጠይቅ ነዉ፡፡

የአገራችንን የመንግስታት ግንኙነት የፖሊሲ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት አብይ እና የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም በማድረግ ነበር ወደ ስራ የተገባው፡፡ በዚህም በሀገራችን የመንግሥታት ግንኙነት ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት፣ ተቋማዊ መዋቅር፣ የአሠራር ስርዓትና ሂደቶች ላይ የዳሰሳ ጥናቶችን በማከናወን በግንኙነቱ ዙሪያ ያሉ ክፈተቶችንና ጥንካሬዎችን የሚያሳይ ሪፖርት የማዘጋጀት ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የመንግሥታት ግንኙነት ዙሪያ የመጀመሪያ ረቂቅ የክፍተት ዳሰሳ ሰነድ በመሆን በባለድርሻ አካላት በውይይት እንዲፈተሽ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የተመረጡ የፌዴራል አገራትን (የጀርመን፣ የሲዊዘርላንድ፣ ሕንድ፣ ካናዳ፣ ደቡብ አፍሪካ) የመንግሥታት ግንኙነት ተሞክሮዎች ተቀምረው  የኢፌዲሪ የመንግስታት ግንኙነቶች መነሻ የፖሊሲ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በዝግጅት ሂደቱ፣ በአስፈላጊነቱና ዓላማው ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና የጋራ መግባባት እንዲፈጥሩ በየደረጃው ሰፊ ወይይቶችንና ምክክሮችን በማድረግ በተካሄዱት የዉይይትና የምክክር መድረኮች ላይ የተገኙ ጠቃሚ ግብዓቶችን በፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ በማካተት የመጨረሻውን ቅርፅ በማስያዝ የኢፌዲሪ የመንግስታት ግንኙነቶች የፖሊሲ ማዕቀፍ መነሻ ሰነድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ምክር ቤቱም ጥቅምት 3 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው 40ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የፖሊሲ ማዕቀፉን በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ የፖሊሲ ማዕቀፉ ለሕዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ የስራ ክፍሉ ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የመንግስታት ግንኙነት ስርዓት የሚመራበት ራሱን የቻለ ህግ ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ በማስፈለጉ ግንኙነቱ የሚመራበትን ረቂቅ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ሕጉ እንዲጸድቅ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኮ በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡