ሥለ ቋሚ ኮሚቴዎች ሥለ ቋሚ ኮሚቴዎች

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በተሻሻለው የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሰራርና የአባላት የስነምግባር ደንብ ቁጥር 3/2013/ በአንቀጽ 72- 76 መሠረት የተደራጁ ቋሚ ኮሚቴዎች እና ተግባራት

1. ቋሚ ኮሚቴዎች

1.1 ምክር ቤቱ የሚከተሉት ቋሚ ኮሚቴዎች ይኖሩታል፡-

ሀ. የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ  ቋሚ ኮሚቴ

ለ. የመንግስታት ግንኙነት፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገመንግስት አስተምሮና ቋሚ ኮሚቴ

ሐ. የበጀት፣ ድጐማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ናቸው፡፡

መ. የሕገመንግሥት ትርጉምና ውሳኔ አፈፃፀም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ

ሠ. ከላይ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ምክር ቤቱ ሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎችን ሊያቋቁም ይችላል፡፡

1.2. ቋሚ ኮሚቴዎች ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቱ ነው::

1.3. እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ፡-

ሀ. ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ በአፈጉባኤው አቅራቢነት ምክር ቤቱ ከአባላቱ መካከል የሚመርጣቸው አሥራ አንድ አባላት ይኖሩታል፡፡ አባላቱ ከመካከላቸው ፀሃፊ ይመርጣሉ፡፡

     ለ. የቋሚ ኮሚቴዎች ፀሃፊዎች በምክር ቤቱ በቋሚነት የሚሰሩ ይሆናሉ፡፡

1.4. አንድ የምክር ቤት አባል በአንድ ጊዜ ከአንድ ቋሚ ኮሚቴ በላይ አባል ሆኖ ሊሠራ አይችልም፡፡

1.5. የቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች ተጠሪነታቸው ለኮሚቴው እና ለአፈጉባኤው ይሆናል፡፡

1.6. የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚከተሉት አጠቃላይ ስልጣንና ተግባራት አሏቸው፡፡

ሀ. በተመሩላቸው ጉዳዮች ላይ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ማቅረብ፤

ለ. የተለያዩ አቤቱታዎች ማስተናገድ፤

ሐ. በቀረቡላቸው ጉዳዮች ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት የመጥራትና የማወያየት፤

መ. የተለያዩ አውደጥናቶችና የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት፤ የልምድ ልውውጥ ማድረግ፤

ሠ. ከምክር ቤቱና ከአፈ ጉባኤው የሚሰጧቸውን ሌሎች ተግባራት ማከናወን፤

2  የቋሚ ኮሚቴዎች ተግባራት

ሀ. የሕገመንግሥት ትርጉምና ውሳኔ አፈፃፀም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ የሚከተሉት ስልጣንና ተግባር ይኖሩታል፤

  1. በሕገመግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በሚቀርቡ የውሳኔ ሀሳቦች ላይ ከምክር ቤቱ ወይም ከአፈጉባኤው የሚመሩለትን ጉዳዮች መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
  2. በሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገመንግስት ትርጉም አያስፈልግም በሚል በተሰጠ ውሳኔ ላይ ማንኛውም ባለጉዳይ ለምክር ቤቱ የሚያቀርበውን ይግባኝ መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
  3. አግባብነት ያላቸው የሕገመንግሥት አተረጓጐም መርሆዎች በምክር ቤቱ ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
  4. የሕገመንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ እንዲጠና በማድረግ ወይም ከምክር ቤቱ ወይም ከሚመለከተው አካል ሲቀርብለት መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
  5. በሕገ መንግሥት ትርጉም እና በውሳኔ አፈጻጸም ክትትል ዙሪያ ጥናትና ምርምሮች እንዲካሄዱ ያደርጋል፡፡
  6. ለተሰጠው ሥልጣንና ተግባር አፈጻጸም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች የሚሰበሰቡበትንና ጥናቶች የሚካሔዱበት ስልት እንዲቀየስ ያደርጋል፡፡ በስራ ላይ የሚውሉበትንም ሁኔታ ያመቻቻል፡፡
  7. የሕገ መንግሥታዊ ውሳኔዎች አፈጻጸም የክትትል ሥርዓት ይዘረጋል፤ ይከታተላል፤
  8. በምክር ቤቱ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡፡

 

ለ. የመንግስታት ግንኙነት፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገመንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡፡

 

  1. በሕዝቦች እኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር የሚያስችሉ ተግባራትን ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን እንዲከናወኑ ያደርጋል፡፡
  2. የመንግስታት ግንኙነት ሥርዓት ተቋማዊ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ይሰራል፡፡
  3. ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ የፍትሐብሔር ጉዳዮች በጥናት እንዲለዩ በማድረግ የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
  4. የፌዴሬሽን ምከር ቤትና የክልሎች የጋራ የምክከር መድረክ ያስተባብራል፤
  5. የመንግስታት ግንኙነት ፎረሞችና አደረጃጀቶች በአዋጅ ቁጥር 1231/2013 መሰረት እየተፈጸሙ ስለመሆናቸው ይከታተላል፣ ምክርና ድጋፍ ይሰጣል፤
  6. የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ አከላለልን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ የሚያቀርበውን ረቂቅ መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
  7. የሕብረተሰቡን ንቃተ-ሕገመንግሥት ለማዳበር የሚያስችሉ ስልቶች እንዲቀየሱና የሕገመንግሥት አስተምሮ በተለያዩ ዘዴዎች እንዲከናወኑ ያደርጋል፡፡
  8. በየደረጃው ያሉት የትምህርት ተቋሞች በሕዝቦች መካከል እኩልነትና አንድነትን የሚያጠናክሩ የትምህርት ዓይነቶች በሥርዓተ ትምህርታቸው ማካተታቸውን ምክር ቤቱ ይከታተላል፡፡
  9. የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሕዝቦች መካከል እኩልነትና አንድነትን የሚያጠናክሩ በቂ ሽፋንና አምድ መመደባቸውን ይከታተላል፡፡ 
  10.  ለሕዝቦች እኩልነትና አንድነት መጠናከር እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ አመለካከቶችና አዝማሚያዎች እንዲጠኑና እንዲለዩ ያደርጋል፤ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
  11. በአገራዊ ማንነት እና በብሔር ማንነት መካከል ሚዛን ለመጠበቅ የሚያስችሉ እርምጃዎችን በጥናት ይለያል፤ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
  12.  ለህብረ-ብሔራዊና አገራዊ አንድነት የሚረዱ ጉዳዮችን በጥናት ይለያል፤ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
  13. ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሚና ካላቸው አካላት ጋር ይሰራል::
  14. አካታች የሆነ የፌደራል የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር የሚያስችሉ እርምጃዎችን በጥናት ይለያል፤ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
  15. በብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች መካከል የመቻቻልና ለጋራ ዓላማ የመሥራት ባሕል እንዲዳብር እንዲሁም አንድነታቸው እንዲጠናከር የሚያስችሉ እርምጃዎችን በጥናት ይለያል፤ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
  16. ልሳነ ብዝሃነት እንዲዳብር የሚያስችሉ እርምጃዎችን በጥናት ይለያል፤ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
  17. ለተሰጠው ሥልጣንና ተግባር አፈጻጸም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች የሚሰበሰቡበትንና ጥናቶች የሚካሔዱበትን ስልት እንዲቀየስ ያደርጋል፡፡ በስራ ላይ የሚውሉበትንም ሁኔታ ያመቻቻል፡፡
  18. በምክር ቤቱ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡

ሐ. የበጀት፣ ድጎማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሥልጣንና ተግባር

  1. በሕዝቦች እኩልነትና በመፈቀቀድ ላይ የተመሰረት አንድነት ስር እንዲሰድና እንዲዳብር እንዲሁም በክልሎች መካከል የተመጣጠነ እድገት ለማምጣት የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል፣ እቅድ ይነድፋል፤ ሲጸድቅም ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
  2. ድጎማና የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈልበትን ቀመር አስመልክቶ በጥናት ላይ የተመሰረተ የውሣኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡ ሲፀድቅም አፈፃፀሙን ይከታተላል፡፡
  3. በሥራ ላይ ያለው የድጎማና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ቀመር አፈፃፀምን እየገመገመ አስፈላጊ የማሻሻያ ሀሳቦችን ለምክር ቤት ያቀርባል፡፡
  4.  የድጎማና የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈልበትን ቀመር ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ መረጃዎች በአግባቡ ተሰብስበው መቀመጣቸውን፣ መተንተናቸውን፣ ትክክለኛና ወቅታዊ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡
  5. ተለይተው ያልተሰጡ የታክስና ግብር የመጣል ሥልጣኖችን አስመልክቶ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን መርምሮ ከሚመለከታቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚቴዎች ጋር በመነጋገር በጥናት ላይ የተመሰረተ የውሣኔ ሃሳብ ለሁለቱም ምክር ቤቶች ያቀርባል፡፡
  6.  የድጎማ ቀመሩ በክልሎች መካከል የተመጣጠነ እድገት እና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል በማምጣት በኩል የተጫወተውን ሚና ለመገምገም የሚረዱ ጥናቶች እንዲጠኑ ያደርጋል፡፡
  7. የገቢ ክፍፍል ወይም የድጎማ ቀመሩን አስመልክቶ አከራካሪ ነጥቦች ሲነሱ ወይም ቀመሩ እንዲሻሻል ጥያቄ ሲቀርብ ለምክር ቤቱ የውሣኔ ሀሳብ ያቀርባል፡፡
  8. የፌዴራል የመሰረተ ልማት አውታሮች ሥርጭት ለኢንቨስትምንት ትርጉም ያላቸው እና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ይዘረጋል፤ ይከታተላል፣ ለምክር ቤቱ ምክረሃሳብ ያቀርባል፡፡
  9. በምክር ቤቱ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡፡

መ. የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡፡

  1. በማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የራስን እድል በራስ ለመወሰን እስከመገንጠል ያለውን መብት በተመለከተ ጥያቄ ሲቀርብ በሕገመንግሥቱና በሌሎች አግባብነት ባላቸው ሕጐች መሠረት መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
  2. ማንኛውም ማህበረሰብ ማንነቴ አልታወቀልኝም፤ ቋንቋዬን፣ ባህሌን እና ታሪኬን የማሳድግበት ሁኔታ አልተመቻቸልኝም የሚል አቤቱታ ሲቀርብ ጥናት እንዲካሄድ ያደርጋል፤ የምክረሃብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፤
  3. ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የራስ በራስ ማስተዳደር መብቴ ተሸራርፏል፤ ቋንቋዬን፣ ባህሌን እና ታሪኬን የማሳድግበት ሁኔታ አልተመቻቸልኝም፣ በአጠቃላይ በፌዴራል ሕገመንግሥት የተደነገገው መብቴ አልተከበረም ወይም በማንኛውም ሌላ ምክንያት አድሎ ተፈጽሞብኛል የሚል አቤቱታ ሲቀርብ ጥናት እንዲካሄድ ያደርጋል፤ የምክረሃብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፤
  4. የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማንነት መገለጫ አትላስ/ፕሮፋይል/ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን እንዲጠና ያደርጋል፡፡
  5. በማንነት፣ በአስተዳደር ወሰን እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ጥናትና ምርምሮች እንዲካሄዱ ያደርጋል፡፡
  6. በክልሎች እንዲሁም በክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን አስመልክቶ ከአፈጉባኤ ወይም ከምክር ቤቱ የሚመሩለትን ጉዳዮች መርምሮ በሕገመንግሥቱና በሌሎች ሕጐች በተደነገገው መሠረት የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
  7. አለመግባባቶችን ለማስወገድ የሚረዱ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ የግጭት መከላከያና ማስወገጃ ስልቶችን በማጥናትና ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የአሰራር ሥርዓትና ስልት ይዘረጋል፡፡ ተቋማዊ ይዘትና አደረጃጀት እንዲኖራቸውም ያደርጋል፡፡
  8. ብሔራዊ የግጭት መከላከልና የሰላም ግንባታ ስትራቴጂ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ያዘጋጃል፤ በተግባር ላይ እንዲውል ያደርጋል፤
  9. የአስተዳር ወሰን ጥያቄዎች የሚፈቱበትን አግባብ ምክረ ሃሳብ ያቀርባል፤
  10.  በቅድመ ሕዝበ ውሳኔ፣ በሕዝበ ውሳኔ ወቅት እና በድህረ ሕዝበ ውሳኔ የአፈጻጸም ሂደት ይከታተላል፤ የሰላም ግንባታ፣ የጋራ የልማት ስራዎች እና መልካም የሕዝቦች የርስ በርስ ግንኙነት እንዲኖር ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመሆን ይሰራል፡፡
  11. የሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣሉ ወይም ሊጥሉ የሚችሉ ጉዳዮች ሲኖሩ በራሱ ተነሳሽነት ወይም በሚመለከታቸው አካላት ሲቀርብለት መርምሮ በጥናት ላይ በመመስረት የችግሮቹን መንስኤዎችና መወሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎች የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
  12. የሕዝብ ብዛታቸው አነስተኛ በመሆኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለየ ውክልና የሚያስፈልጋቸው ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይለያል፤
  13. በምክር ቤቱ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡፡