የፌዴሬሽን ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ መስከረም 29 ይጀመራል
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛው የፓርላማ ዘመን አራተኛ ዓመት የሥራ ጊዜ የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባውን መስከረም 29 እና 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ያካሂዳል፡፡ ከዚህ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባኤያቸውን የሚያካሄዱም ይሆናል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁለቱ ቀናት ጉባኤው ከሦስቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚቀርብለትን የውሳኔ ሃሳቦች ተወያይቶ ውሳኔውን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሕገ መንግሥት ትርጉም አኳያ በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ተብለው የቀረቡለትን እንዲሁም የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም ተብለው ይግባኝ የቀረበባቸው አቤቱታዎችን መርምሮ ውሳኔውን ያሳልፋል፡፡
በሌላም በኩል ምክር ቤቱ በበጀት ድጎማና በጋራ ገቢዎች ድልድል ዙሪያ የተዘጋጀው ሕጋዊ ማዕቀፍ ላይ ተወያይቶ ይወስናል፡፡ በተመሳሳይ ባለፈው አመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ የፌዴራል የመሠረተ ልማት አውታሮች ሥርጭት ፍትሃዊነትን አስመልክቶ ያስተላለፋቸው አቅጣጫዎች አፈፃፀም ሪፖርትን ከገመገመ በኋላ ተጨማሪ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ይሆናል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ምክር ቤቱ የሦስቱን ቋሚ ኮሚቴዎች ዕቅድ ላይ ተወያይቶ የሚያጸድቅ ይሆናል፡፡