የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሀገራቸውን ህልውና የማስጠበቅ ሀለፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ገለጹ።

ኅዳር 05/ 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ፦ /በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት/

ኢትዮጵያ የማይታለፉ የሚመስሉና ታሪክ የማይረሳቸው በርካታ ፈተናዎች አሳልፋ ለዓለማችን የጥቁር ህዝቦች የነፃነትና የኩራት ተምሳሌት በመሆን እዚህ ደርሳለች በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገልጸዋል።

እንደ ክቡር አፈ ጉባዔው ገለጻ የኢትዮጵያ ሀገር ወዳድ ልጆች በሁሉም ፈተናዎች ሳይበገሩ፣ በልበ ሙሉነት አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው የሀገራቸውን ታሪክን በደማቸው ቀለም ጽፈው ኢትዮጵያን ከነሙሉ ክብሯ ለትውልድ አስተላልፈዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ትናት የተደራጀ የጦር መሳሪያ ስንቅ ሳይኖራቸው የውጭ ወራሪን አሳፍረውና አንገቱን አስደፍተው የመለሱት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዛሬም እንደ ትናንቱ የአባቶቻችንን ጀግንነትና ወኔ በመላበስ ጠላቶቻችን በመቅበር ታሪክን መድገም ይገባናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተሰማራንበት መስክ ሁሉ የራሳችንን አኩሪ ታሪክ የምንጽፍ እንጂ የታሪክ ተወቃሽ መሆን አይገባንም ብለዋል።

አያይዘውም የተከበሩ አፈ ጉባዔው ዛሬም አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በውጭና በውስጥ ኃይሎች ድጋፍ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የጭካኔ በትሩን በግልጽ ማሳረፍ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋቶች እያደረሰ በመሆኑ መላው ሕዝባችን እነዚህን ጠላቶች በማሸነፍ ኢትዮጵያን ማሻገር ይገባዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችንና በወራሪው ኃይል ለተጎዱ ወገኖቻችን አለኝታነተቸውን በማሳየት ለውጥና ለውጭ ጠላት ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ አሳይተዋል ብለዋል።

አያይዘውም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ልበ ሙሉ ሆነን፣ ጀግነነታችን የምናድስበት፣ የሰመዓታትን አደራ የምንዘክርበት፣ የኢትዮጵያን ክብር የምናስቀጥለበት፣ ከታሪክ ተወቃሽነት ራሳችንን የምናድነበት ጊዜው አሁን ነውና አገራችንን እናስቀድም ህልውናችንን እናስቀጥል ብለዋል።

“ወንድማማችነት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት''!