የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ንግግር

የተከበራችሁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዮች!

ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች!

ክቡራትና ክቡራን!

ከሁሉ በማስቀደም በሕገ መንግሥታችን መሠረት በተካሄደው ስድስተኛው አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተወክላችሁ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቤት ወደሆነው ምክር ቤት በመምጣታችሁ የተሰማኝን ደስታ በራሴና በኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስም ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

ክቡራትና ክቡራን አኔን በዛሬው ዕለት ምክር ቤቱን እንድመራ ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ እጅግ አመሰግናለሁ፡፡

መላው የአገራችን ሕዝቦች በታሪካቸው ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂደው በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባራት እንዲከናውኑ ወክለው ሲልኳችሁ በቀጣዩቹ አምስት ዓመታት አገራችንን በዕድገትና በብልጽግና፣ በሰላምና በዴሞክራሲ ጎዳና እንድትራመድ ቁልፍ ሚና ልትጫወቱ ትችላላችሁ ከሚል እምነት ነው፡፡ ይህንንም በዛሬው ዕለት በተግባር ጀምራችሁታል፡፡

 

የተከበራችሁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት!

ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች!

ክቡራትና ክቡራን!

ሁላችንም እንደምናውቀው ያሳለፍናቸው ጥቂት የለውጥ ዓመታት የአገራችንን ዕድገትና ሰላም በማይፈልጉ የውስጥ ተላላኪዎችና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እጅግ የተፈተንበት፣ ታላላቅ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ሚዲያዎች እንኳን ሳይቀሩ “ኢትዮጵያ ፈርሳለች!” በማለት ትናጋቸው እስከሚሰነጠቅ ድረስ የአለቆቻቸውን ከንቱ ማላዘን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተጋባት ሌት ከቀን የተጉበት፣ ይህንንም ተከትሎ በሕዝባችን ላይ ሞትና አካል መጉደል፣ ንብረት መውደምና መፈናቀል፣ ስጋትና መጠራጠር በሰፊው የታየበት፣ በአንጻሩ ደግሞ በዚህ ክፉ ጊዜ ያልከዱን መልካም አሳቢዎቻችንና ታሪካዊ ወዳጆቻችን በዓለም የፍርድ አደባባይ ኢትዮጵያ ስለምትከተለው የፍልስፍና መንገድ ጥብቅና ቆመው የተከራከሩበትና አሸናፊ የሆኑበት፣ በውጭም በአገር ውስጥም ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው አገራቸውን ለማሻገር ሌት ከቀን የታተሩበት፣ በ6ተኛው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሀገራዊ ምርጫ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያሳዩት የጨዋነትና የአርቆ አሳቢነት ተግባር ደምቆና ፈክቶ የወጣበት፣ በዚህም ወዳጆቻችን የተደሰቱበት፣ አገር ሻጪዎችና ደላላዎች አንገታቸውን የደፉበትና ቅስማቸው የተሰበረበት ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡

በሕዝብ የተመረጠው መንግሥትም በየደረጃው ባካሄደው የመንግሥት መሥረታ ውስጥ ሁሉንም አካታች በሆነ መንገድ አስፈፃሚ አካላትን ለማዋቀር ጥረት ያደረገበትና ሀገራችን አዲስ የዲሞክራሲ ምዕራፍ ለመጀመር ቁርጠኝነቷን በተግባር ለዓለም ማኅበረሰብ ያሳየችበት፣  የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ በአደናቃፊዎችና በክፉ አሳቢዎች በእጅጉ የተፈተነ ቢሆንም አሸናፊነቱን ግን ማስቆም አለመቻሉን ማሳየት የተቻለበት፣ ይልቁንም ፈተናዎቹ ተጨማሪ ትምህርትና ፅናት ሰጥተውት ለሕብረ ብሔራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓታችን ጥንካሬና ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአንድነት መሠረት ለመጣል የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ማገልገሉን መመልከት ችለናል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ አስቸጋሪና የፈተና ወቅት የማይሳኩ የሚመስሉ ታላላቅ ድሎች ያስመዘገብንባቸውና እንደ አገርም ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የአሸናፈነቷም አንዱ ማሳያ ዛሬ በዚህ የጉባኤ አዳራሽ ተሰባስበን ስለአገራችን መጻኢ እድል መምከር መጀመራችን ነው፡፡  

የተከበራችሁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት!

ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች!

ክቡራትና ክቡራን!

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ካለፈው ረዥም የአብሮነት ታሪካቸው በጎ ተሞክሮዎችን በመጠበቅ፣ በመከባበር፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት የኢ... ሕገ መንግሥትን  በጋራ ተወያይተው አጽድቀዋል፡፡

የሕብረ ብሔራዊ አንድነት መገንቢያ መሠረቱ አብሮና ተባብሮ ለመኖር መወሰን ነው፡፡ በአብሮነትና በትብብር ለመኖር ደግሞ ብዝኀነትን አምኖ መቀበል ይጠይቃል፡፡ ብዝኀነት በአግባቡ ለተገነዘበውና አምኖ ለተቀበለው እድል አንጂ ዕዳ አይደለም፡፡ አባቶቻችንን “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኀኒቱ” የሚሉትም ብዝኃነትን በአመክንዮ ለማሳየት ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ነው፡፡ ብዝኀነት ከማንነቶች ፍላጎት የሚመነጭ አገራዊ አንድነት መገንቢያና የጥንካሬ ምንጭ እንደሆነም ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በመሆኑም ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት ለማንነቶች የተሟላ መብት ማጎናጸፍ ይጠይቃል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ራሳቸውን የማስተዳደር ሙሉ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች፣ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እኩል እንደሆኑ ተደንግጓል፡፡ ቋንቋዎች እንዲሁ እኩል ናቸው፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ሆነዋል፡፡ የጾታ እኩልነት ተከብሯል፣  ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፌዴሬሽን /ቤት ተመጣጣኝ ውክልና አግኝተዋል፡፡  ይህ የእኩልነት መብት ለሕብረ ብሔራዊነት አንድነት የማይናወጥ አምድ ሆኖ ያገለግላል፡፡

ስለሆነም በኢትዮጵያ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር የማንነቶችን ሉአላዊነት ማረጋገጥ፣ በየደረጃው በሚገኙ የሥልጣን እርከኖች ፍትሐዊ ውክልናን መስጠትና በመካከላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ትስስር ማጎልበት ይገባል፡፡

በመሆኑም የተጀመረው የሕብረ ብሔራዊ አንድነት በጽኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይሁንታ አግኝታችሁ ወደዚህ ምክር ቤት የመጣችሁ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅባችኋል፡፡

የተከበራችሁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት!

ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች!

ክቡራትና ክቡራን!

በአንድ አገር የሕግ የበላይነት መኖሩ ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች አንዱ መንግሥት፣ የመንግሥት አካላት እና ዜጎች በሕግ ጥላ ስር ሲወሰኑና ሕግን ሲያክብሩ፣ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶችም ዋስትና ማግኘት ሲችሉ ነው፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ “በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነፃ ፍላጎታችን በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት” በሚል የሕግ የበላይነት ለሃገራችን ግንባታ ወሳኝ እንደሆነ ይገልፃል፡፡

የሕግ የበላይነት አለመኖር የሕዝቦች ፈቃደኝነት እንዲቀንስ ስለሚያደርግ የአንድነት መሠረት ይናጋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሰጠው ሥልጣንና ተግባራት መካከል አንዱ የሆነውን “በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ስር እንዲሰድና እንዲዳብር ያደርጋል” የሚል ነው፡፡ በመሆኑም ምክር ቤቱ የሕግ የበላይነት በሚያስከብሩ ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል እላለሁ፡፡

በመጨረሻም መጪው ዘመን ለሀገራችን ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ አንድነት ጥንካሬ፣ እድገትና ብልጽግና ከልብ እየተመኘሁ፣ ለተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!

 

                     አመሰግናለሁ!