ሠላም ፣ መቻቻል መከባበርና አብሮነት ለአገር ግንባታ

ሠላም መቻቻል መከባበርና  አብሮነት  ለአገር  ግንባታ

 ግንቦት 02/2011 . የኢ... የፌዴሬሽን  ምክር ቤት ከኢፌዴሪ ሳይንስና  ከፍተኛ  ትምህርት  ሚኒስቴር  ጋር  በመተባበር  ሠላም ፣መቻቻል  መከባበርና  አብሮነት  ለአገር ግንባታ  በሚል  ርዕስ ከአገሪቱ 54 የመንግስት  ዩኒቨርስቲዎች  ለተውጣጡ  ዪኒቨርስቲ ማህበረሰብ  የውይይት  መድረክ  በማዘጋጀት  የግንዛቤ  ማስጨበጫ  ውይይት  አካሂዷል፡፡ ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት  አፈ-ጉባዔ የተከበሩ / ኬሪያ ኢብራሂም በዜጎች /በተማሪዎች/ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ከስሜት ነፃ ሆኖ በውይይትና በሃሳብ ልዕልና መፍታት ለዘላቂ ሠላም ወሳኝ መሆኑን በማስመር ተማሪዎች ከጊዜያዊ ችግር ይልቅ ለዘላለማዊ አገራቸው ህልውና ማሰብ ቀዳሚ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡   

በማስቀጠልም  ዘመናትን  የተሻገረው አገር በቀል የሠላም፣  የመቻቻል፣  የመከባበርና  የአበሮነት  እሴቶች  በአገሪቱ  አስተማማኝ  ሠላም  እንዲረጋጋ፣የተጀመሩ  ልማቶችን ለማስቀጠል ፣የጋራ  ተጠቃሚነትን  ለማረጋገጥ  ወሳኝ መሆኑን  አሥምረዋል፡፡ ስለሆነም  ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ  ማንነቶች፣ ቋንቋዎች፣ባህሎችና ሃይማኖቶች ያላቸው ማህበረሰብ  ስብስብ በመሆናቸው  እንደትንሿ  ኢትዮጵያ ተደርገው   ይወሰዳሉ፡፡ እነዚህን  ብዝኃነቶችን  በአግባቡ  በማስተናገድ  ሠላም፣ መከባበር፣ መቻቻልና  አብሮነት ሥር  እንዲሰድና  እንዲጠናከር  ከዚህም በላይ እሴቶቹን  በመጠበቅ  ለተተኪ  ትውልድ በማስተላለፍ  ረገድ  ዩኒቨርስቲዎች ከፍተኛ  ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ  አኳያ የመምህራንና የተማሪዎች  ሚና  ከፍተኛ  እንደሆነም   ተቀምጧል፡፡ 

እሴቶቹን  ለአገር ሠላምና  ልማት  ግንባታ  እንዴት  መጠቀም  እንደሚገባና  ለማህበረሰቡ   ማሸጋገር እንደሚቻል  ሃሳብ ተሰጥቷል፡፡ ይህ እንዲዳብር የዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣   መምህራንና  ተማሪዎች ተነሳሽነት ማሳየት ወሳኝ ነው፡፡  ሠላም ለሁሉም  ነገር መሠረት ነው  የሚሉት  ተማሪዎቹ አንዳንድ  መምህራን  ራሳቸውን  ቢያዩ  የሚል አስተያየት  በመስጠት የታዘቡትን   አካፍለዋል ፡፡

 አስተማማኝ ሠላም ከማስፈን  አንፃር  ክልሎች፣ዞኖች ፣ወረዳዎች ከዩኒቨርሲቲ  ውስጥ ካሉት ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች  ማለትም  ከተማሪዎች ሕብረትና  ከሠላም  ፎረም ጋር ተቀራርቦ  መሥራት  እንደሚገባ  ተጠቁሟል፡፡ እነዚህን  አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩ  በሚያስፈልገው  ቁሳቁስና  በጀት  መደገፍና  ክትትል ማድረግ  የተፈለገውን ዓላማ  ስኬታማ ከማድረግ ረገድ ድርሻው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን በተመለከተም የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕርዝዳንት ባቀረቡት ጽሑፍ የዩኒቨርሲቲውን የሠላም፣ የመከባበርና የመቻቻል እሴቶች አተገባበር ተመክሮ አካፍለዋል፤ በአስተማርነቱም አድናቆት ተችሯል፡፡

ለሰላም ቅድመ ሁኔታ  የለውም ሊሰጠውም  አይገባም  የሚሉት  ተማሪዎቹ የጥላቸ  ፖለቲካ ሰውን ከሰው  እየለያየ  አገሪቱን  ለአደጋ እያጋለጣት መሆኑ  ቢታሰብበት በማለት በአጽንኦት አሳስበዋል ፡፡

አገራችን የራሷ የሆነ አገር በቀል የሠላም  እሴቶች  ያላት  ስትሆን ይህ እየተሸረሸረ መምጣቱ  ለችግር አጋልጧታል፡፡ ስለሆነም  የአገር ሽማግሌዎች የግጭት  አፈታት ልምድ ፣የሃይማኖት  መሪዎች አስተምሮና  የአርቲስቶች  ሚና  ጐልተው  እንዲወጡ  ከመንግስት  መዋቅርና  ከዩኒቨርስቲዎች በቅንጅትና በትኩረት  እንዲሰሩ  ማበረታታት  ይጠበቃል፡፡ ይህ  እንዲሆን  ሁሉም  ኃላፊነት  እንዳለው  አሳስበዋል፡፡የሠላም  እሴት የተሳካና ዘመን  ተሻጋሪ  እንዲሆንም  ከአንደኛ ደረጃ   እስከ ፕሪፓራቶሪ ባሉ የትምህርት ካሪክለም  ሥርዓት  አካል   ቢደረግ የሚል አስተያየት  ሰጥተዋል፡፡

ግጭት ሥራ በፈታው የሰው  አእምሮ ውስጥ የሚፈጠር መጥፎ  መንፈስ ስለሆነ ለሥራ አጦች የሥራ ዕድል፣ከሥራ መልስም  ወይም በእረፍት  ጊዜ  የሚዝናኑበት ቦታዎች ቢመቻቹና  ለሚነሱ  ጥያቄዎች አፋጣኝ  ምላሽ ቢሰጥበት  መልካም  እንደሚሆን  ተጠቁሟል፡፡ አመራሮችም  ቢሆኑ ኃላፊነትንና  ተጠያቂነትን ለመቀበል  ተነሳሽነት  እንዲኖራቸው ይገባል፡፡

 በመጨረሻም  እንደመፍትሄ  ሊወሰዱ  የሚገባው  መንግስት  ሕግን  የማስከበር ሚና  በሚገባ እንዲወጣ፣ በሕዝብ  ላይ ግንዛቤ መፍጠር፣ኢትዮጵያዊ  እሴቶችን  አሳልጦ መጠቀም በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጣልቃ ገብነት  እንዲቀር፣ የየአካባቢን ህብረተሰብ ያካተተ የሠላም አማካሪ ምክር ቤት  እንዲቋቋም፣ እንደ ዩኒቨርስቲ ዶክተሮች/ምሁራን/አስተያየት  በተቋማት ውስጥ የሰላም ሥጋት ተጋላጭነትን የሚያባብሱ  እንደውስጣዊ  መሠረተ ልማቶች/መብራት ፣ውሃና ሌሎች/ አቅርቦቶች እንዲሻሻሉ፣የሥራ አጥነት ዕድልን  በየትም  በማንም  ማጥበብ፣አቅም ያላቸውን ኢንቨስተሮችብን መጋበዝ ፣የሕዝብ  ግንኙነትን ማጠናከርና የመሳሰሉ  እሴቶችን  ማጎልበት ግጭቶችን  ይቀንሳል  ወንድማማችነትን/እህትማማችነትን  እና መተሳሰብን እንደሚያጠናክር አስተያየቶች ተሰጥቶበታል፡፡