የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግስት አተረጔጐም መርሆችን በተመለከተ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን  ምክር ቤት የሕገ-መንግስት  አተረጔጐም  መርሆችን በተመለከተ  ለባለድርሻ  አካላት ግንዛቤ  ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ

ቅዳሜ ሰኔ 15/2011 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን  ምክር ቤት የሕገ-መንግስት  ትርጉም ምንነት የትርጉም መርሆዎችና ዘዴዎች የሕግና የሥነ-ሥርዓት  ጉዳዮች  በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ከድሬደዋ ከተማ  መስተዳድር ፣ከሀረሪ ፣ ከሶማሌ ክልሎች ለተውጣጡ  ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

ሥልጠናውን  በንግግር የከፈቱት  የተከበሩ   አቶ መሐመድ  ረሽድ ሃጂ የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን  ምክር ቤት ም/አፈ-ጉባኤ  ሲሆኑ የዓውደጥናቱ ዓላማ በህገ-መንግሥት  ትርጉም መርሆዎችና ምክር ቤቱ  ውሳኔ በሰጠባቸው  የተመረጡ የህገ-መንግስት ትርጉም ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ  እንደ  ሆነ አብራርተዋል፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግም  ባለድርሻ  አካላቱ የምክር ቤቱን ሚና በመረዳት እና በማሳወቅ  ሂደት   የበኩላቸውን  ድርሻ  እንዲወጡ  ለማስገንዘብ ነው ብለዋል፡፡

ሕገ- መንግስትን የመተርጐም ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምከር ቤት የተሰጠበትን ዋና ምክኒያት ሲያብራሩ የህገ-መንግስቱ  ባለቤቶች የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና  ህዝቦች እንደመሆናቸው መጠን  ከእነርሱ የተሻለ  ተርጔሚ አይኖርም በማለት ለፌዴሬሽን  ምክር ቤት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ  በጀመሪያዎቹ  ዓመታት ወደ ፌዴሬሽን  ምክር ቤት  ይመጡ የነበሩ  አቤቱታዎች  በጣም ጥቂት  እንደነበርና  ነገር ግን አሁን የዜጎች ንቃተ- ሕገ-መንግስት እያደገ  ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በርካታ ውስብስብ ጉዳዮች  ወደ ምክር ቤቱ እንደሚመጡና  ከነዚህም  ውስጥ እጅግ በጣም ጥቂት  አቤቱታዎች  ብቻ ሕገ- መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቻዋል ተብለው  ውሳኔ  የሚሰጥባቸው ሲሆን  አብዛኛው  ግን እንደፍርድ ቤቶች  ይግባኝ መልክ ይይዛሉ ፡፡ይህም ዜጐች  በትርጉም ዙሪያ የግንዛቤ  እጥረት  እንዳላቸው የሚያመለክትና  ከምክር ቤቱም በኩል  ግንዛቤ በመፍጠር ሂደት  ክፍተት መኖሩን  አብራርተዋል፡፡ ይኽኛውም መድረክ ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት  ታስቦ የተዘጋጀ  መሆኑን  አስረድተዋል፡፡

የሕገ- መንግስት አተረጔጐም  መርሆዎችን  በተመለከተ ስለኢትዮጵያ  ሕገ-መንግስት ባህሪያት ፣የሕገ- መንግስቱን የበላይነት ስለማስከበር፣የሕገ-መንግስት ትርጉም አሰጣጥ የራሱ የሆኑ  መርሆዎች  ስለመኖሩ፣ የሕገ-መንገስት ትርጉም  ከግለሰቦች  ፍላጐት/ideology/ ነፃ መሆን ስላለበት ሁኔታ እና ሕገ-መንግስት ተርጔሚው ሕገ-መንግስቱን  የማሻሻል ሥልጣን የሌለው  ስለመሆኑ ጽሑፍ አቅራቢው የዘርፉ  ምሁር የሆኑት ዶ/ር  ጌታቸው  አሰፋ የአዲስ አባበ ዩኒቨርስቲ  መምህር አስረድተዋል፡፡

 በመጨረሻም ጥናታዊ  ጽሑፉን የሚያጠናክር አስተማረነት ያላቸውን በሕገ- መንግስት  አተረጔጐም መርሆዎች ላይ ያተኮረ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ-መንገስት  ትርጉም የተሰጠባቸውን የተመረጡ  አቤቱታዎች በፌዴሬሽን ጽ/ቤት የሕገ-መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ያውቃል በቀለ አማካነት ቀርበው ውይይት  ተደርጐባቸዋል፡፡ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ከተሳታፊዎች  በኩል የተሰጠባቸው ሲሆን ወደፊት ለሚደረጉ  ማሻሻያዎች እንደግብዓት እንዲያገለግሉ ተወስደዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ መድረክ በትግራይ፣ በአማራና በከፊል ኦሮሚያ ክልሎች  መካሄዱን አውስተው  ጠቃሚ ግብዓቶች መገኘታቸውን የተከበሩ ም/አፈ-ጉባኤው  ተናግረዋል፡፡