የሕገ-መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮና ስርፀት ስትራቴጂ

ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በፖለቲካዉ፣ በኢኮኖሚዉና በልማቱ የሰራነዉን ያህል ሕገ-መንግስቱንና የፌዴራል ስርዓቱን በማስገንዘብ በኩል የተሰራው ስራ ውስን በመሆኑ ዜጎች መብትና ግዴታቸዉን በሚገባ ጠንቅቀዉ እንዳያዉቁ ከማድረጉም በላይ የራሳቸዉን መብት ለማስጠበቅ በሚል ሽፋን የሌሎችን መብት ሲጥሱና በማህበራዊ እና የቴክኖሎጂ ተፅዕኖ ቁጥጥር ስር ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ወጣቱን ጨምሮ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች በዉጭ ኃይሎች የተሳሳተ ትምህርት እየተወሰዱ በስርዓቱ ትክክለኛነት ላይም ጥያቄ እያነሱ ይገኛሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የአስተምህሮቱ ስራ በተደራጀ፣ በተቀናጀና ተቋማዊ በሆነ አግባብ ወጥነት ባለዉ መልኩ የሚሰጥ ሳይሆን በተበጣጠሰና በተንጠባጠበ መልኩ እዚህም እዚያም በመሰጠቱ ምክንያት ሕብረተሰቡ በሕገ-መንግስቱና በፌዴራል ስርዓቱ ላይ እኩል ግንዛቤ እንዳይኖረዉ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም እነዚህን ክፍተቶች በጥናት በመለየት ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ምክርቤታችን ከዴሞክራሲ ተቋማትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከሰራቸዉ አንኳር አገራዊ ስራዎች መካከል አንዱ የሕገ-መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምሮና ስርፀት ስትራቴጂ ነዉ፡፡

ስትራቴጂው በሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆችና እሴቶች ላይ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን በሚገባ አውቆ ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር መራመድ የሚችል በምክንያትና በውይይት የሚያምን ዜጋ ለመፍጠር፣ የዲሞክራሲ ባህልን ለማዳበርና የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማጎልበት፣ የመቻቻልና አለመግባባቶችን በሰላምና በውይይትና የመፍታት ባህል ለማሳደግ እንዲሁም ሕገ-መንግስቱንና የፌደራል ስርዓቱን በተናጠል ሳይሆን ተቀናጅቶና ተናቦ ለማስረፅና ተደራሽ ለማድረግ ያለዉ ፋይዳ ከፍተኛ ነዉ፡፡

በዚህ ረገድ የስራ ክፍሉ የእስከአሁኑ የአስተምህሮ ስራችን ምን እንደሚመስል የነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳ በማድረግ፣ የሌሎች አገሮችን ልምድ (ታንዛኒያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ የጀርመንና ሲዊዘርላንድ) በመቀመርና ከአገራችን ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር ለአገርና ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የሕገ-መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምሮና ስርፀት ስትራቴጂ በማዘጋጀት የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በዝግጅት ሂደቱ፣ በአስፈላጊነቱና ዓላማው ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና የጋራ መግባባት እንዲፈጥሩ በየደረጃው ሰፊ ወይይቶችንና ምክክሮችን በማድረግ፤ በተካሄዱት የዉይይትና የምክክር መድረኮች ላይ የተገኙ ጠቃሚ ግብዓቶችን በስትራቴጂው ውስጥ በማካተት የመጨረሻውን ቅርፅ በማስያዝ የሕገ-መንግትና ፌደራሊዝም አስተምህሮና ስርፀት ረቂቅ ስትራቴጂ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ምክር ቤቱም ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው 41ኛ መደበኛ ስብሰባ አስተምህሮና ስርጸቱን በብቃት ወደ ማህበረሰቡ ለማድረስ የሚችል ተጠሪነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሆነ ጠንካራና ውጤታማ ተቋም በማቋቋም ቀደም ሲል የነበረውን ወጥነት የሌለው አሰራር በማስተካከል በተደራጀ መንገድ ለመምራት የሚያስችል የሕገ-መንግሥትና ፌደራሊዝም አስተምህሮና ስርጸት ተቋም እንዲቋቋምና ስትራቴጂው በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ የስራ ክፍሉ የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምሮ ተቋም አደረጃጀትና የደመወዝ እስኬል በማስጠናትና የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ተቋም ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት አዋጁ እንዲፀድቅ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኮ በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡